አንቀፅ-17 ነፃነት/ባርነት * ከአድዋ-ጎሎጎታ
ይህ ታሪክ ከተፈፀመ እነሆ በዛሬዉ 122 ዓመቱን ይዟል፡፡ ይህ ቀን ለአሁኗ ኢትዮጲያ ማንነቷን ያስጠበቀችበት ከባርነት ራስዋን ነፃ ያደረገችበት ቀን ነዉ፡፡ ከመላዉ የአለም ሃያላን የተነሳን ከባድ የባርነት በትር በፅኑ ትግል ከጫንቃዋ ያነሳች ብሎም ለመላዉ የአፍሪካ ሀገራትና ህዝቦች የነፃነት ምክንያት ነበረች፡፡ እስቲ ከምክንያት ጋር ለማየት እንዲረዳን የዚህን ታሪካዊ ስፍራ ስያሜና ለዚህ ታሪካዊ ጦርነት መነሻ የነበረዉን ነገር እናንሳ፡፡ የአድዋ የስሙን ትርጓሜ ከ ጣሊያናዊዉ ኢትዮጲያን ወዳድ ሪቻርድ ፓንክረስት ከተፃፈዉ ፅሁፍ ብንመለከት አድዋ ማለት (village of the awa) ማለትም “የአዋዎች መኖሪያ” ማለት ሲሆን ይህ ስፍራ ለ ንግድ ስራ ለረጅም ጊዜያት ምቹ ስፍራ ሆኖም አገልግሏል:: ብሎም ለነገስታት ዋና መቀመጫቸዉና ከተለያዩ የአለም ክፍላት የሚመጡ ሰዎችን መቀበያ ሰፍራቸዉም ሆና አገልግላለች ፡፡ለነዚህ ሁሉ ነገር ተፈላጊ ያደረጋት ምክንያትም ያላት መልካምድራዊ አቀማመጥ ለዚህ ሁሉ ነገር ምቹ ስፍራ አድርጓት ቆይቷል፡፡እንዲሁም ትልቁ የመገባቢያ ስፍራም ነበረች በ 1890እ.ኤ.አ በ አዉግስጦስ ቢ.ዌይልድ የአድዋን የገበያ ስፍራ ከተመለከተ በኃላ “ሁሉንም የምርት አይነቶችን ፈልጎ ማይታጣባት” ሲል ገልፆታል፡፡በቴክኖሎጂዉም ዘርፍ ቢሆን ከ አስመራ-አዲስ አበባ የተዘረጋዉ የቴሌግራፍ መስመር ያለፈባት ሲሆን በዚህም ምክንያት ቢሮዉን በዛ ስፍራም ለመክፈት ተችሏል፡፡ ብሎም የቴሌግራፍ አገልግሎት ለትግራይ ክልል ያስገየችም ነበረች፡፡እናም በዚህ ስፍራ ይደረጉ ለነበሩ የልማት ዝርጋታዎች የጣሊያን መንግስት የተለያዩ ስራዎችን በዚሁ አካባቢ ላይ ከኢትዮጲያ መንግስት ጋር በመተባበር ሰርቷል፡፡ ለአብነትም የቴሌግራፍ ዝርጋታዉን ያከናወኑት ጣሊያናዊያን ነበሩ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኃላ የዚህን ስፍራ አመቺነት ብሎም ኢትዮጲያን በቅኝ ግዛቷ የመያዝ ፍላጎቷ ተዳምረዉ በነበሩ የተለያዩ የልማት ድርድሮች ዉስጥ ለዚህ ታሪካዊ ጦርነት ምክንያት የነበረዉ የዉጫሌ ስምምነትን ለማድረግ በተዘረዘሩት የህብረ ስምምነት ዉል ዉስጥ የፀብ መነሻ የሆነን ሃሳብ በጣሊያኖች የተጨመረዉ፡፡ ይህም በ 1889እ.ኤ.አ በብዙ የሃገሬ ሰዎች የምትታወቀዉን የአንቀፅ-17 የኢትዮጲያን ሉዓላዊትነትና ነፃ ሀገርነትን ጥያቄ ዉስጥ ብሎም አደጋ ዉስጥ የከተተ አንቀጽ ነዉ፡፡ የሰዉን ልጅ ገና በፍጥረቱ መጀመሪያ ላይ ከፈጣሪዉ የተነገረዉን ትዕዛዝ ትርጉሙን በመለወጥ ነፃነቱን በባርነት ለወጠበት፡፡ ይህንኑ መንገድ ጣሊያን ተጠቀመችበት የጣሊያኑን ትርጉም ኢትዮጲያ ከዉጭ ሃገራት ጋር የሚኖራትን የዉጪዮሽ ግንኙነት በጣሊያን መልካም ፍቃድ ላይ ብቻ የተመሰረት አርጎ ማቅረብ ነበር፡፡ በዚህ የእጅ አዙር የባርነት ህይወት ላለመያዝ የቆረጡት አባት አርበኞችና መሪዎች በክተት አዋጅ ሀገሬዉን በሙሉ ወደ ጦርነት ጠሩ፡፡ በዚያን ዘመን ጣሊያን በአድዋ ላይ እጅግ ከፍተኛ የጦር ሰራዊት ከነሙሉ የምግብ ስንቅ ይዘዉ ሰፍረዉ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጲያ ጦር በቅጡ እንኳን የተደራጀ ካለመሆኑ በተጨማሪ ከጣሊያን ጦር ጋር ዉጊያ አድርጎ ድል ማድረግ ደግሞ የማይታሰብ ነገር ነበር ግን ጦርነትን አማራጭ የሌለዉ አማራጭ ሆኖ ነበርና ወደ ትጥቅ ትግሉ መግባት አይቀሬ ሆነ፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያት ነጻነት ነዉ ባርነትን ካለመፍቀድ መብትን በሌሎች እጅ አሳልፎ ያለመስጠት ጽኑ ትግል፡፡ ነጻነት ለሰዉ ልጅ ህይወትን የሚያስገበር ትልቅ ጥያቄዉ መሆኑን የሚያስረዳን ወቅት ሆኖ ተመልክተናል፡፡ አየህ አንባቢዬ ሆይ ጣሊያን ብትገዛን ኖሮ እንዲህና እንዲህ ይኖረን ነበር ሊሉህ ይችላሉ ግን ሆድ ቢሞላ ነፃነት ግን ከሆድ ያለፈ የዉስጥህ ሃያል ድምፅ ያላት ጩኸት ነች፡፡ለዚህም ነዉ ከዛሬ 122 ዓመት በፊት በአድዋ ጦርነት ሀገሬ ልጆችዋን የገበረቸዉ፡፡በዚህም ጦርነት ማለትም 1896 እ.ኤ.አ ከማለዳዉ አንስተዉ ረፋድ ላይ ድል በመንሳት ዉድ ዋጋ ያላትን ነፃነት ይሏት ነገርን ለትዉልዳቸዉ ብሎም ለመላዉ የአፍሪካ ሀገር በስጦታ መልክ የሰጠችዉ፡፡(በዚህ ዉስጥ አንድ ነገርን መመልከትም እንችላለን ጥልያንን ያህል ትልቅ ጦር ሀገሬዉ ሁሉ በዘሩ በሃይማኖቱ ሳይከፈል በአንድነት ባይዘምትበት ነፃ ይሏትን ሀገር ሰላም ይሏትን ዉድ ነገር ማስጠበቅ ባልተቻለ ነበር ለዘመኔ ወጣት ለሆንከዉ ለዚህ ትዉልድ ምክሬ በትዉልድ መዝገብ ላይ ማይሻር ታሪክ ፅፈህ ማለፍ ትፈልጋለህ እንግዲያዉስ መከፋፈሉን ትተህ እንደ አንድ ህዝብ በችግርህ ላይ ዝመትበት ድል ያንተ ነዉ፡፡ ይህን ቀን ሳስብ በታሪክ አጋጣሚ ዉስጥ የ2000 ዓመት ታሪክ ያለዉ ከአድዋም ጦርነት በአይነቱ የሚመሳሰል ለነፃነት የተደረገን አንድ ጦርነት አሰብኩ፡፡ ይሄ አሁን የምልህ ጦርነት ግን ከባድ መሳሪያን ያነገበ ህዝብ ከህዝብ ጋር ያደረገዉ አልነበረም እዉነት ነዉ የኢትዮጲያ ጦር አቅሙን አይቶ ቢነሳ ቀድሞም ራሱን በገዛ ፍቃዱ ለባርነት ባስገዛ ነበር ነገር ግን ለነፃነታችን ሲባል ባርነትን በደም ዋጋ ተከፍሎለት ማስጠበቅ ተቻል፡፡ ይሄ ከ2000 ዘመን በፊት የነበረዉ ጦርነት ከዚህ ሚለየዉ ግን አንድ ሰዉ ስለ ትዉልዶች ነፃነት ሲል የከፈለዉ ዋጋ ነዉ፡፡ አንዱ ስለ ሁሉ የሞተበት፡፡ይህ ሰዉ አለም ሳይፈጠር ጀምሮ የሰዉን ልጅ ከፈጠረዉ ከፈጣሪዉ(ከአባቱ) ዘንድ የተሰጠዉን ነፃነት አጥቶት በባርነት ሲመላለስ ሲኖር እየተመለከተ ይህን አይቶ ማለፍ ያልቻለ ፍቅር ግድ ያለዉ ነዉ፡፡እንደ ሃገሬ ለባርነት መግዣ ልትዉል እንደነበረችዉ ትርጉሟ እንደተቀየረችዉ አንቀፅ 17 ሁሉ በምድር ሁሉ ያለን የሰዉ ልጅ በትዉልድ መጀመሪያ የነበሩትን አዳምና ሄዋንን በባርነት ሊገዛ የወደደዉን የነፍሳቸዉን ጣሊያን ከሰሪዉ እጅ የተሰጠዉን ትዕዛዝ እንደ አንቀፅ 17 ትርጉሙን በመቀየር ካታለለ በኃላ ከህግ በታች በማድረግ የሰዉን ልጅና አለሙን ሲመራና ሲያዝ ለአያሌ ዘመናት በሀጢያት ባርነት ሲገዛና ሲያስተዳድር ኖረ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኃላ ይህ ሰዉ ከላይ ከአባቱ ዘንድ ሆኖ ሲባዝን የነበረዉን የሰዉን ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ክብር ሊመልሰዉ ወዶ ከዚህ የሃጢያት ባርነት መዉጪያ ብቸኛ መንገዱ እርሱ እንደመሆኑ ፍቅር ግድ ብሎት ስጋን ለብሶ ከነበረዉ ክብር በእጅጉ አንሶ ዛሬ እንደምናስበዉ የሀገሬ ታሪካዊ ቀን ህዝብን ሁሉ አስተባብሮም ሳይሆን ዋጋ ሊከፍልለት የመጣለት የሰዉ ልጅ ራሱ ሳይቀበለዉ ቀድሞ ወደነበረበት ክብራቸዉ ሊመልስ በደሙ ስለሃጢያታቸዉ የሚገባዉን ደመወዝ ሊከፍል ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ልክ የሃገሬ አርበኞች በአድዋ ተራራ ላይ ባርነትን ወግድ እንዳሉት እንዲሁ ይህ የሰዉ ልጅ ራሱን በጎሎጎታ ተራራ ላይ እንደ በግ ታርዶ ስለ ሰዉ ልጅ ሲል በሰዎች ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ሰዉ ከላይ ከሰራዉ እጅ የተሰጠዉን የቀደመ ክብሩን መለሰለት፡፡ ትርጉሙ የተቀየረበትን አንቀፅ መልሶ በደሙ ጻፈዉ፡፡በቅዱስ ዮሃንስ ወንጌል በምዕራፍ-19 ላይ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን “ኢየሱስንም ይዘዉ ወሰዱት መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎሎጎታ ወደ ተባለዉ የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ በዚያም ሰቀሉት እየሱስም ሆምጣጤዉን ከተቀበለ በኃላ ተፈጸመ አለ”:: አዎ ተፈፀሟል አንዳች ሳይቀር የሰዉን ልጅ ከሃጢያት ቅኝ ግዛት ዕዳዉን ሙሉ ከፍሎ ነጻነትን እንዲሁ በነፃ ሰጥቶታል፡፡   ይህ ነዉ ይሉሃል ፍቅር ነፍሱን ስለ ወዳጁ አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርሰ!!! አየህ አንባቢዬ ነፃነት እንዲህ እጅግ ታላቅ ዋጋ ያላት ነገር ናት እንኳንስ ይቅርና ለሰዉ ልጅ ለፈጠረክ ፈጣሪክም ጭምር፡፡ ትክክለኛዉ ነጻነት ይህ ነዉ በአለም የሚገይ ጊዜያዉ ደስታ ሳይሆን፡፡ለዚህም ነዉ በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ ነፃ አወጣን የተባለዉ!!! እኔ አበቃሁ በዚህ የሀገሬ የድል ቀን ላይ ቆመህ/ሽ ይህን አስብ/ቢ ነፃነትህን/ሽን ማን ወሰደዉ??? በዚህ ጊዜ ወርቅ በሚባልበት ዘመን ይህችን ጥሁፍ ማንበብ ጊዜያችሁን ካለማባከን ቆጥራችሁ አንዳች ቁምነገር ይኖረዉ ይሆንን ብላችሁ ስላያችሁት ክብረት ይስጥልኝ ብያለሁ!!!

                                                        ምስጋና ክብረት

Comments

Post a Comment